Abstract:
የዚህ ጥናት አብይ አላማ በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በትብብር መማር ለመጻፍ ችሎታና ተነሳሽነት
ያለውን አስተዋጽዖ መመርመር ነበር፡፡የጥናቱ ንድፍ መጠናዊ ምርምርምር ላይ የተመሰረተ ከፊል
ሙከራዊ የጥናት ንድፍን የተከተለም ነበር፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የጯሂት ከፍተኛ ሁለተኛ
ደረጃ ትምህርትቤት በአመች ምክንያት የናሙና አመራረጥ ዘዴ ተመርጧል፡፡በዚሁ ትምህርት ቤት
ከሚገኙ 6 የዘጠነኛ ክፍል ምድቦች ውስጥ ሁለቱ ተመርጠው ቅድመ ትምህርት የመጻፍ ችሎታ
መመዘኛ ፈተና ከተፈተኑ እና የመጻፍ ተነሳሽነት የጽሑፍ መጠይቅ ከሞሉ በኋላ በመካከላቸው የጎላ
ልዩነት አለመኖሩ ተረጋግጧል፡፡ በመቀጠል ምድቦቹ በእጣ ንሞና ዘዴ የቁጥጥርና ሙከራ ቡድን
በመባል እንዲሰየሙና ለሁለት እንዲከፈሉ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት የሙከራ ቡድኑ በትብብር
መማር ዘዴ የመጻፍ ትምህርትን እንዲማሩ ሲደረግ፤ የቁጥጥር ቡድኑ ደግሞ እየተተገበረ ባለው ዘዴ
የመጻፍ ትምህርትን እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ ሁለቱ ምድቦች በተለያየ መማር ዘዴ የመጻፍ ትምህርትን
እንዲማሩ ከተደረገ በኋላ በድህረ የመጻፍ ፈተና እና በጽሑፍ መጠይቅ መረጃዎች እንዲሰበሰቡ
ተደርጓል፡፡ ከቁጥጥርና ሙከራ ቡድኑ የተሰበሰቡ የፈተናና የጽሁፍ መጠይቅ መረጃዎች ዝርዝር
ዓላማዎቹን ለማሳካት በሚያስችል መልኩ በነጻ ናሙና ቲ-ቴስትና ጥንድ ናሙና ቲ-ቴስት በመጠቀም
በየምድባቸው ተተንትነዋል፡፡ የነጻ ናሙና ቲ-ቴስት ቡድኖቹን አንዱን ከሌላው በተመሳሳይ ተላውጦ
ለማወዳደር ያገለገለ ሲሆን የጥንድ ናሙና ቲ-ቴስት ደግሞ እያንዳንዱን ቡድን በተመሳሳይ ተላውጦ
ከራሱ የቀደመ ተላውጦ ጋር ለማወዳደር ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በጥናቱ ውጤትም በአማርኛ ቋንቋ
መጻፍን በትብብር መማር የተማሪዎችን የመጻፍ ችሎታና ተነሳሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው
ታውቋል፡፡ በቀጥታ ውጤቱ ይገለጽ፡፡ ይህም በሙከራና በቁጥጥር ቡድኖች መካከል የታየው የድህረና
ቅድመ ትምህርት ፈተና ውጤት በሳይንሳዊ ዘዴ ተተንትኖ በተገኘው ውጤት የተረጋገጠ ሲሆን
ለምናልባት ስህተት 5 መቶኛ (ፒ 0.05) በመተው ወይም 95 ፐርሰንት እርግጠኛ በመሆን በተሰራው
ስሌት መሰረት ተመርምሯል፡፡ በሁሉም የሙከራና ቁጥጥር ቡድኑ የአማካይ ውጤት ሳይንሳዊ
ንጽጽሮች ሰንጠረዡ ላይ የተመዘገበው (ተሰልቶ የተገኘው) የጉልህነት ደረጃ (0.000) በማነጻጸሪያነት
ከተጠቀምንበት የስህተት ይሁንታ (0.05) በእጅጉ አንሶ ተገኝቷል፡፡ ከዚህም የምንረዳው እየተተገበረ
ካለዉ የማስተማር ዘዴ ይልቅ የመጻፍ ክሂልን በትብብራዊ መማር ዘዴ ማስተማር ለተማሪዎቹ
የመጻፍ ክሂል ችሎታና ተነሳሽነት መሻሻል ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ነው፡፡ ከጥናቱ ውጤት
በመነሳት ትብብራዊ የመማር ዘዴ ተግባራዊ እንዲደረግና የአማራ ክልል ትምህርት
ቢሮ፣የሚመለከታቸው የትምህርት መምሪያዎችና ባለሙያዎች ለተግባራዊነቱ የሚያስፈልጉ የቁሳቁስ፣
ክህሎትና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ እንዲሰሩ አጥኝዋ መክራለች፡፡